Friday, September 4, 2015

የህወሃት ኢህአዴግ ጉባኤ የልማት ጉባኤ ሊሆን አይችልም!



በ1967 ዓ/ም የጀመረውና በትግራይ ህዝብ ተነሳሽነት የተካሄደውን የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ የትጥቅ ትግል፣ ከ1968 መስራች ጉባኤ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 12 ጉባኤዎች አካሂዷል፣ ማንኛውም ጉባኤ ሲካሄድ ውስጣዊ አሰራሩና አመራሩ በብቃትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ስራዎችን ለማስፈፀም፤ የአገሪቱ የእድገት ደረጃ ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማሸጋገር፤ በህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት፤ የዜጎች መብትና ነፃነት ለማስከበር፤ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥና ባጠቃላይ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ተብሎ ነው።
    ነገር ግን እስካሁን ከተካሄድዉ የህወሃት ኢህአዴግ ጉባኤዎች ማንኛውም ለውጥ ሲመጣ አልታየም። በአሁኑ ግዜ ለህዝባችን በብሄርና በዘር ለያይቶ በጥርጣሬ አይን እንድንተያይ የተወሰነውን “የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚልና ሌሎች ፀረ ህዝብ ውሳኔዎች የተደነገጉበት ባለፉት የድርጅቱ ጉባኤዎች ነው።
    እነዚህ ለረጅም ግዜ ስልጣን እንደ መዥገር ተጣብቀው የህዝባችን ደም እየመጠጡ የሚገኙትን አብዛኛዎቹ መሪዎች፣ መሰረታቸው የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች ናቸው፣ እነዚህ ከድሃ  ህብረተሰባችን እየነጠቁ የግል ሃብታቸውን እያካበቱ የሚገኙ መሪዎች፣ በ1977 ዓ/ም የኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈና እንደ ቅጠል እየረገፈ በነበረበት ወቅት ከውጭ አገሮች ለህዝብ ተብሎ የመጣውን የእህል እርዳታና ገንዘብ እኛ ነን የምናከፋፍለው በማለት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማሌሊት ምስረታና ለሌሎች ወታደራዊ ስራዎች ማስፈፀምያ እንዲውል ያደረጉ መሪዎች ናቸው።
   የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣኖች ከነበራቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድና ውስጣዊ ያለመተማመን፣ በ1993 ዓ/ም ወደ ሁለት በተከፋፈሉበትና፣ የድርጅታችን ውስጣዊ ሁኔታ በስብሷል፤ ገምቷል ብለው በተናገሩበት ሰዓት፣ በወቅቱ አሁን በስልጣን የሚገኙት አመራሮቹ ሳይቀሩ አምነው እንደተቀበሉትና በተለያየ መድረኮች እንደተናገሩበት ይታወቃል። የሚያስገርመው ግን እስካሁን ድረስ በስብሰውና ገምተው እንዲሁ እስካሁን መቅረታቸው ነው፣ ምናልባት ያመጡት ለውጥ ካለም ራሳቸው ባሰባሰቡት መጨረሻ የሌለው ሃብት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው በተንደላቀቀ ሂወት እንዲኖሩ ማስቻላቸው ነው።
    የመጣው ለውጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራሩ ወደ ዜሮ ደረጃ ማውረድ፤ ሃቅን ይዘው የሚከራከሩ ሰዎችን መግደልና ከስራ ውጭ በማድረግ ተኮላሽተው እንዲቀሩ ማድረግ፤ በኢንቨስትመንት ስም ለም የእርሻ መሬት ከድሃ ገበሬዎች በመንጠቅ ለውጭ ባለሃብቶች መስጠት፤ ባጭሩ ለውጡ እድገት የሚያሳይ ሳይሆን ወደ ኋላ የሚመልስ፤ ወደ ፊት የሚራመድ ሳይሆን ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ከፋ ሁኔታ የሚመልስ እንደሆነ አጠቃላይ ህዝቡ እያየው ያለ ሁኔታ ነው።
    በአሁኑ ግዜ ዓለማችን እድገት እያሳየች ባለችበት ግዜ፣ በአንጻሩ ህዝባችን ግን፣ ገና ከኃላቀርነት ሳይወጣ በተላላፊ በሽታዎች እየተሰቃየና ህይወቱን እያጣ ይገኛል።በለጋሽ አገሮች ለድሃ ማህበረሰቡ ተብሎ የሚመጣውን መድሃኒት በውድ ዋጋ እንዲሸጥ በማድረግ፣ በቂ ህክምና ሳያገኝ ቀርቶ ለሞት መብቃቱ ለህወሓት ኢህአዴግ መሪዎች እድገት ነው፣ ዴሞክራሲያዊያን ድርጅቶች በደህንነት ኃይሎች እንዲዳከሙ በማድረግና ስልጣን እንደ ርስት ተይዞ ሩብ ክፍለዘመን በቂ አይደለም ቀጣይም አገሪትዋ እኛ ነን የምናስተዳድራት ማለታቸው። ለህወሃት ኢህአዴግ መሪዎችና ጭፍሮቻቸው እድገት ነው።
    ህወሃት 12 ጉባኤዎች በማካሄዱ ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አልቻለም ብቻ ሳይሆን፣ 24 ዓመት ሙሉ የህዝቡን ትእግስት ያሟጠጠ ስርአትም ነው። እናም ለውጥ ለማምጣት ከሆነ ስርዓቱ በማስወገድ ሌላ ህዝባዊ ስርዓት ሲቀየር ብቻ ስለሆነ፣ አሁንም እንዳለፈው ክንዳችን በማስተባበር በጸረ ህዝብ ስርዓት ላይ ትግላችን በተጠናከረ መንገድ ስናስቀጥልና፣ የደርግ ስርዓት ያስወገደውን ፀረ ግፈኞች አፈሙዛችንን ወደ ህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች ማዞር ስንች ብቻ     ነው።
ምክንያቱም በህወሃት ኢህአዴግ ጉባኤዎች የሚመጣ አንዳችም ለውጥና ልማት ስለማይኖር።