Tuesday, July 16, 2013

የሽረ-እንዳስላሰ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የክፍል ሃላፊዎችንና ሰራተኞችን ከሃላፊነታቸው የማውረድና የማሰር እርምጃ መውሰዱን የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።



በደረሰን ዘገባ መሰረት በያዝነው ሳምንት በሽረ-እንዳስላሰ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት በወንጀል ምርመራ ስራ ተመድበው ሲያገለግሉ የነበሩ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊዎችና ሰራተኞች ህዝቡን በቅንነት የማያገለግሉና ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም በሙስና ተዘፍቀው የማይገባቸውን ሃብት ሲያካብቱ የቆዩ ሲሆን፥ ግለሰቦቹ በጉቦና በጥቅማጥቅም እንደሚሰሩ በከተማዋ ኗሪ ህዝብ በተደጋጋሚ የተገመገሙ ቢሆኑም የህዝቡን ቅሬታ በመናቅ በያዙት ቦታ እንዲቀጥሉ ተደርጓል፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ወንጀለኞችን ሸፋፍኖ ለማለፍ በማይችሉበት ሁኔታ ስለደረሱ  የፖሊስ ጽ/ቤት የበላይ ሃላፊዎች እርምጃ ለመውሰድ ተገደዋል።
በዚህ መሰረት በከተማ ከሃላፊነታቸው የወረዱና ከስራ እንዲባረሩ የተደረጉ የፖሊስ አባላትና አመራሮች መካከል ፣-
1-ዋና ኢንስፔክተር ክብሮም መሓሪ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ የነበረ በሙስና በተደጋጋሚ የተገመገመና ከሃላፊነት ወርዶ በተራ መርማሪ እንዲሰራ የተደረገ።
2-ሙሉ በርሀ ዋና መርማሪ የነበረና በተደጋጋሚ ተገምግሞ ከሃላፊነቱ ወርዶ ተራ የፖሊስ አባል ሆኖ እንዲያገለግል የተወሰነበት
3-ጋሻው ከወንጀል ምርመራ ተነስቶ በሌላ ቦታ ተመድቦ በተራ ፖሊስ አባልነት እንዲሰራ የተደረገ
4-ብርሃነ ሽሻይ የተባለ መርማሪ ከትህዴን ጋር ግንኝነት አለህ በሚል ሰበብ በተደጋጋሚ የታሰረና የተፈታ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከስራው እንዲባረር የተደረገ።
የመልካም አስተዳደር ጭላንጭል የማይታይበት የህወሓት-ኢህአዴግ ስርዓት አንድ በሙስና የተጨማለቀን ሰው በነበረበት ስራ እንዳይቀጥል ህጉ የሚከለክል መሁኑ እየታወቀ የስርዓቱ ባለስልጣናት ግን ህግን በመጣስ ሙሰኞችን ከነበራቸው ደረጃ በማውረድ በነበሩበት ስራ እንዲቀጥሉ ስለሚያደርጉ መላው የከተማዋ ኗሪ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅሬታውን በተደጋጋሚ ከመግለጽ አልፎ በስርዓቱ ላይ ያለውን ተቋዎሞ በመግለጽ ላይ ስለሚገኝ የህዝቡን ተቃውሞ ለማለዘብ ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ነው ሳይሆን አይቀርም በማለት ታዛቢዎች ይናገራሉ።