Monday, May 26, 2014

ግንቦት 20ን ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ( ት.ህ.ዴ.ን ) የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ



ወደ ኋላ መለስ ብለን ያለፈውን የ17 አመት የትጥቅ ትግል ስናስታውስ የኢትዩጵያ ህዝብ በተለይም ደግሞ ያ ደማዊ ጦርነት የተካየደበት ትንግርታዊ ፅናትና ጀግንነት ከሁሉም ብሄረ ብሄረሰቦች ጋር በማበር፤ ከትንሽ ንብረቱ እስከ መተኪያ የሌላት ክቡር ሂወቱን ሰጥቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መስዋእትና የአካል ጉዳት የከፈለ የትግራይ ህዝብ፤ የደርግ-ኢሰፓን ስርአት ደምስሶ የትጥቅ ትግሉ ድል ካደረገ እንሆ 23 አመታት አስቆጥሮ ይገኛል።
   ለ17 አመታት ያክል የተካሄደው የትጥቅ ትግል አላማውና የተከፈለው ሁለንትናዊ መስዋእትነት ደግሞ ሰላም፤ ዴሞክራሲንና ፍትህን የሚያነግስ፤ በብሄር-ብሄረሰቦች አንድነትና እኩልነት አምኖ ዴሞክራስያዊ ስርአት ለመገንባት፤ ከወገንተኝነትና አድልዎ ነፃ የሆነ፤ የመላው የኢትዩጵያን ህዝብ ጥቅም የሚያስቀድም ህዝባዊ መንግስት ለመትከል ነበር።
   ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የታገለለት አላማ ከግንቦት 20/ 1983 ዓ/ም ማግስት ጀምሮ ለአማታት ይመኘው የነበረ የታገለለትን አቛምና የተሰዉ የሰማዕታትን አደራ በስልጣን ላይ ባሉት ካድሬዎችና የሕ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ባለስልጣናት ትርጉም የለሽ ሆኖ ተዳፍኖ ቀርቷል።
    የሕ.ወ.ሓ.ት-ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች በህዝቦች መስዋእትነትና ስንክልና የስልጣናቸውን ወንበር ከአደላደሉ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ በግልኝነትና በሙስና  በከፋ መልኩ ደግሞ መልካም አስተዳደር ጠፋ፤ ፍትህ በጉቦና በእከከኝ ልከክልህ ሆነ፤ ህዝባችን የኢትዮጵያ ህዝብ በከፋ መልኩ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ወድቀህ ትገኛለህ።
    የተከበርክ ህዝባችን እነዚህ በስምህ እየነገዱ ያሉ ግን ደግሞ የማይወክሉህ በሙስና አዘቅት የተዘፈቁ የሕ.ወ.ሓ.ት-ኢ.ህ.አ.ደ.ግ ባለስልጣናት የሚመሩት ስርአትና አደረጃጀታቸው በመፈራረስ ላይ እንደሚገኝ ይህ ደግሞ በላይህ ላይ እየተፈፀመ ያለው በደልና ግፍ የውድቀታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን መዘንጋት መሳት የለብህም።
    ስለሆነም ነው ዜጎቻችን ከቀያቸው ያለ ቅድመ ዝግጅትና መረዳዳት ሊፈናቀሉ አይገባም፤ ብሄር ከብሄር የሚያጋጭ ዘረኛ የሆነ አስተዳደር እያስተዳደራችሁ ወደ ትውልድ የሚያልፍ ጥላቻ አትመስርቱ፤ የህዝብ ድምፅ  እየደፈናችሁ ዴሞክራሲ አለ አትበሉ፤ ብለህ ሃቅ ሰለነገርካቸውና ሌሎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብትህን በማንሳትህ ብቻ ህዝብ እየጨፈጨፉ ስልጣናቸውን ለማራዘም የሚሞክሩ የፌደራል ፖሊስና፤ የአግአዚ ኮማንዶዎችን በመላክ ህይወትህንና የልጆችህን ህይወት እየቀጠፉ ይገኛል።
 ይህ ተግባር የደርግን ስርዓት ህዝብ በሚቃወመው ግዜና ወደ ትግል ሜዳ በሚጎርፍበት ሰዓት ለዚህ የትግል እንቅስቃሴ ለማገት ሲል ይወስድ የነበረው የተስፋ መቁረጥ እርምጃ ጋር የሚመሳሰል ነው። የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓትም በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ስም እየማለ በህዝብና በሃገር ላይ እያደረገ ያለውን እኩይ ተግባር በመቃወም እየተካሄደ ያለው ሁለተናዊ ትግል ከጎኑ በመሆን እንደሚደግፍና የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት ትህዴን ያረጋግጣል።
በተመሳሳይ ውትድርና ክቡር የሞያ መስክ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፣ ስለዚህ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአንድ ሃገር መከላከያ ሰራዊት የሃገር ሉዓላዊነትና ህገ-መንግስት እንዳይጣስ የሚያስከብር፤ ሃገሪቱን ከሚያስተዳድራት ፓርቲ ጋር የማይወግን፤ ለህዝቡ ሰብዓዊና ዴሞራሲያዊ መብት የሚጣበቅ ደልዳላ ሃይል መሆን ይገባል።
በሃገራችን እየታየ ያለው የመከላከያ ሰራዊት ተግባር ግን ከላይ ሆነው የሚያዙት የህወሓት ኢህአዴግ አባላት የሆኑ ከፍተኛ መኮነኖች የህዝብ ዋልታና መከታ ከመሆን ፋንታ በህዝብ ላይ ኣሰቃቂ ግፍ እየፈፀመ መጥታል እየቀጠሎትም ይገኛል።
ይህ በሲቪሉ ማህበረሰብ  ብቻ እየተፈፀመ ያለ ሳይሆን  ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በመጠየቅህ ብቻ በላይህ ላይም በደል እያወረደ በተለያዩ ወታደራዊ እስር ቤቶች ታጉረህ እየተሰቃየህና እየተገደልህ ነው ያለኸው።
ስለዚህ በየክፍልህ ሁነህ የምታደርገውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ድርጅታችን ትህዴን የሚከታተለውና ለተግባራዊነቱ  ከጎንህ ስላለ የታጠቅኸውን መሳሪያ ወደ ከፋፋዩ የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት እንድታዞረውና ለራስህና ለህዝብህ በመሆን እንዲሁም ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር በመወገን ሃገርህን ከነዚህ በሙስና ከተዘፈቁት ግለኞችና  አባገነኖች እንድታላቅቃት የትግራይ ህዝብ ዴምክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት ትህዴን በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ በመላው ሃገራችን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የምትገኙ ዜጎቻችን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳችሁ ለራሳችሁና ለህዝባችሁ እንዲሁም ለሃገራችሁና በድህነት ምክንያት ለራሳቸው ሳይማሩ  ያስተማራቹህ  ወላጆቻችሁን እንዳታግዙ ስርዓቱ እየተከተለ ባለው የተጣመመ የትምህርት ፖሊሲ። ህልማችሁና ራእያችሁ ስኬታማ  ሊሆን አልቻለም።
ስለዚህ እየቀጠላችሁት ያለው ፀረ ወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ላይ ያነጣጠረ  ተቃውሞና ለህዝባችሁ እየከፈላችሁት ያለው መስዋትነት በድርጅታችን የትህዴን ማህደር ልዩ ቦታ እንዳለው እያስገነዘብን ድርጅታችን ትህዴን እያደረጋችሁት ባለው የትግል ጉዞ እያደነቀና እያመሰገነ ለምታደርጉት ሁለተናዊ እንቅስቃሴ ከጎናችሁ እንዳለ ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት (ትህዴን) ህዝብ ከቀያችን አንፈናቀልም፤ ቤታችንን አናፈርስም፤ በመሬት አስተዳደር ያለው አድሎ ይቁም፤ የመሰለህን ሃሳብ የመግለፅ የመደራጀት መብታችን ይረጋገጥ፤ በማለት በየግዜውና በየአቅጣጫው እያደረገ  ያለውን ጸረ የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ተቃውሞ እንደሚደግፍና ከጎናቸው እንደሚቆም ደግሞ ደጋግሞ በአንክሮ ይገልፃል።
ወያኔ ኢህአዴግ ከስልጣኑ መገርሰስ የሚችለው በተናጠል እየተካሄደ ባለው ትግል ሳይሆን አንድነትና ጥምረት በመፍጠር መሆኑን አምኖ ድርጅታችን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ለተግባራዊነቱ ሳይሰላች ሰርቷል እየሰራም ይገኛል፣ አሁንም አንድነትና ጥምረት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመግለፅ ሁላችንም ፀረ ህወሓት ኢህአዴግ እየታገልን ያለን ድርጅቶች ወደ አንድ የትግል ጎራ መሰባሰብ እንዳለብን ድርጅታችን በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ለማጠቃለል በውስጥና በውጭ የምትገኝ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ  ጸረ ህወሓት ኢህአዴግ ለሚደረገው ሁለተናዊ ትግል በግል ይሁን በተደራጀ መንገድ እያደረጋችሁት ያለውን መተጋገዝ በማድነቅ ይበልጥ ደግሞ ከትክክለኛና ዲሞክራሲያውያን ድርጅቶች ጎን ሁናችሁ መተባበርና መታገል ግዴታና ህዝባዊ ሃላፊነት መሆኑን በማመን በተጠናከረ መልኩ እንድትቀጥሉበት ትህዴን ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለጭቁኖች
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ድርጅት ትህዴን
ግንቦት 20/2006 ዓ.ም