የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በነሀሴ ወር ኣጋማሽ 2004 ዓ.ም. መሞታቸውን ተከትሎ በአገራችን
የተተካው አዲሱ አመራር ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ተጥሎ የነበረው ተስፋ ተዳፍኖ በመቅረቱ ተጨባጭ የሆነ
የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሃሳብን የመግለጽ፤ የመደራጀት’ና በሰላም የመሰብሰብ
ነጻነት ላይ የጣሉትን ጥብቅ ገደብ ማስፈጸማቸውን የቀጠሉበት ሲሆን የሲቪል ማህበራትን’ና ነጻ መገናኛ ብዙሃንን እንቅስቃሴ ለማዳከም
አፋኝ ሕጎችን ይጠቀማሉ ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችንም ፖለቲካዊ መነሾ ያላቸውን ክሶች በመመስረት የጥቃት ዒላማ እያደረጓቸው ይገኛሉ።
መንግስት በተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች
ላይ ጣልቃ መግባቱን የተቃወሙ ንፁኃን ወገኖቻችን በጸጥታ ሃይሎች የዘፈቀደ እስር፤ እገታ፤ ድብደባ’ና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች
በላያቸው ላይ ፈፅሞባቸዋል፣ የታሰሩትን የተቃዋሚ አባላትና መሪዎች የፍርድ ሂደታቸው ለህዝብ፤ ለመገናኛ ብዙሃን’ና ለቤተሰቦቻቸው
አባላት በይፋ አልተገለፀም፣ እጅግ አወዛጋቢና መሠረታዊ ግድፈት ያለባቸውን ድንጋጌዎች በያዘው የሃገሪቱ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ
መሰረት ጥፋተኛ የተባሉ የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ገቢ’ና ከውጭ
በሚመጣ እርዳታ በሚደገፉ ስፋት ያላቸው የልማት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ምክንያት የተለያዩ ማህበረሰብ ተወላጆች ያለበቂ ምክክር ወይም ምንም አይነት ካሳ ሳይከፈላቸው
ከመኖርያቸው እንዲፈናቀሉ ከማድረጋቸው በላይ የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪዎችን
ከመኖሪያ ቀያቸው አንስተው ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ሃይል፤ ማስፈራሪያ‘ና ዛቻ እየተፈፀሙ እንደሆኑ ሁሉም ያገሬው ህዝብ የሚያውቀው
ጉዳይ ነው።
በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት በተመለከተም
ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር የሚይዙት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ተከታታይ ህዝባዊ
ተቃውሞ ማድረጋቸውና ይህንን የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ለመግታት መንግስት ሃይልን በመጠቀም የዘፈቀደ እስር እና ድብደባ በተቃዋሚዎቹ
ላይ መፈጸሙና አሁንም እየቀጠለበት መሆኑን ይታወቃል።
ስርዓቱ ባጸደቀው የሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት ክስ በተመሰረተባቸው የተቃውሞ
እንቅስቃሴ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽመዋል፣ ይህ ፀረ ህዝብ ድርጊት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱን መገናኛ ብዙሃን፤
ዲፕሎማቶች፤ የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ህዝቡም እንዳይከታተለው ዝግ በማድረግ ንፁሃን ዜጎቹ በእስር ላይ እያሉ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ
እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በተለያዩ ግዚያት ተደጋግሞ ተነግሯል።
እነዚህ ንፁኃን ወገኖች ጠበቃ እናዳያገኙና
ከቤተዘመድ ጋር ለመገናኘት የነበረውን ችግር ጨምሮ የፍርድ ሂደቱ በሕግ በተቀመጡ ስርዓቶች አግባብ መካሄዱን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ
በርካታ ግድፈቶች ተፈጽመዋል፣ በተከሳሾቹ ላይ በመንግስት ቴሌቪዥን ውንጀላ እና ክስ ያለበት መረጃ በማስተላለፍ መንግስት ተከሳሾቹ
ከፍርድ ውሳኔ በፊት መብታቸውን የሚጋፋ ድርጊት መፈፀሙና መንግስታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጅሃዳዊ ሃረካት የሚል ርዕስ ያለው
የፊልም ፕሮግራም በማስተላለፍ የተከሳሾቹ የፍርድ ሂደት ከመጀመሩ በፊት በቁጥጥር ስር እያሉ የተቀነባበረ ክፍል እንዲታይ መደረጉና
ከነዚህ በመነሳት ፕሮግራሙ የተቃወሙት መሪዎችን እንደ አሸባሪዎች በመቁጠር የሙስሊሞቹን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከአክራሪ የእስልምና
ሃይሎች ጋር በማነፃጸር በላያቸው ላይ ግፍና ሰቆቃ እንዲፈጸም ተደርጓል።
ለማጠቃለል! በአገራችን ውስጥ ያለው የሰብአዊ
መብት ሁኔታ እንደመንግስት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኢህአዴግ ስርዓት ስልጣን ከያዘበት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መሻሻል ሳያሳይ
ለ24 ዓመት ያህል ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህርያቱ ከቀን ወደቀን በማጠናከር እየሄደበት ያለ ሁኔታ መሆኑን አውቀን ትግላችን አጠናክረን
ማስቀጠል ይገባናል።