Thursday, April 24, 2014

የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የ2007ቱ የምርጫ ዝግጅት



      ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ በገሃዱ አለም የሚታዩበትን የሃጢያት ቀዳዳዎች በውሸት ህልማዊ ምናብ የሚደፍን እያስመሰለ በማጭበርበር እድሜ ዘላለሙን እየረገጠ እየጨቆነና እያሳደደ ለመኖር የማይሸርበው ሴራ፥ የማይጠነስሰው የጥላቻ ጥንስስና የማይፈጥረው ፈጠራ የለም፣ ግሩም ፈጣሪ፥ ልዩ ጠንሳሽ፥ ምርጥ ሌባና አሪፍ አጭበርባሪ የተሰኙት የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አለም-አቀፋዊ መጠሪያ ታርጋዎቹ ናቸው።
      በሃገሪቱ ባሳለፋቸው 23 ዓመታት ውስጥ በርካታ አስቂኝ፥ አስገራሚ፥ አዝናኝ፥ ድንቅና ተዓምረኛ የተባሉ የስርቆትና የጭቆና ፈጠራዎች በተለያዩ የዓለማቀፉ መድረኮች ሳይቀር እጅግ ልዩ የተሰኙ የምሁራንን ጆሮ የሳቡ አስደማሚ ገሃዳዊ የሚመስሉ ግን የማይጨበጡ የማታለያ ቀመሮችን እየቀመሩ በሃገሪቱ ዲሞክራሲ ነፃነትና ፍትህ ሞልቶ የተትረፈረፈ ማስመሰላቸውና የኢትዮጵያን እድገት ለማይፈልጉ ሃገራት የስለላ መርብ መዘርጊያ ገመድ መሆናቸው ለማንም ግልፅና ብሩህ ነው።
    በመሆኑም የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ/ምና ግንቦት 15 ቀን 2002ዓ/ም በተካሄዱት ተመሳሳይ የማጭበርበሪያ ምርጫዎች የአጋጠመውን ህዝባዊ ተቃውሞና ጥላቻ እንደመልካም ተሞክሮ በማየት የ5 ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማለት የስርቆታቸው ምስጢር ለህዝብ እይታ ስውርና በሮቻቸው በቀላሉ ሊታዩ የማይችሉ የዘረፋ ፈጠራዎችን በየአቅጣጫውና በየቦታው ዓይነት፥ ጊዜና መጠን የማይለካቸው አሃዳዊ የውሸት ቀመሮችን ፈበረኩ።
      የተቀመሩት ምናባዊ የልማት ቀመሮች አይደለም ከኢትዮጵያ አብራክ የወጣ አበሻዊ ፍጡር ይቅርና የሲዖል ሊቀመንበር ሰይጣን እንኳን የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና አይቃወመውም በተለይ በ5 ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያልተካተተውና ዛሬ በህዝብ ተሳትፎና ትብብር እየተሰራ ያለው የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቁ መፈንቅለ ድህነት በመሆኑ ማነኛውም ለውጥ ፈላጊ ዜጋ ሁሉ የበኩሉን አስተዋጽአ  ሊያበርክት እንደሚገባ እያስገነዘብሁ። ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ግን “ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለው ሁሉ የቀመራቸው የ5 ዓመት የተሰኙ ግን 8እና 9 ዓመት ሊጠናቀቁ የማይችሉ፤ ተፈፃሚ የሚመስሉ ግን የማይፈፀሙና በህዝብ አዕምሮ በቀላሉ የሚሰርፁ ለዘረፋ አመቺ የሆኑት የገንዘብ መሰብሰቢያዎች ተጠናቅቀው አዲሱና ወርቃማው ዘዴ አባይን መገደብና ከተለያዩ ደሃ ሃብታም ሴት ወንድ ህፃን አረጋዊና መነኮሳትን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ደጋፊ ኢትዮጵያውያን በቀረበላቸው ህዝባዊ ጥያቄ መሰረት ሁሉም ከአፉ ሞጭቆ የኢትዮጵያን እድገት በመሻት እየለገሰው ያለውን የግንባሩን ወዝ የአደራ የፀሎት ገንዘብ ዛሬስ በትክክል በስራ ላይ ለማዋል ይሆን የተቀረፀው ምናልባት ነገስ አባይ ተገድቦ ለኢትዮጵያ ህዝብ አገልግሎት ሊሰጥ ይሆን ወይስ ህዝቦቻቸውን ሸጠው ለሚበሉ ስልጣን ወዳድ ስግብግብ አመራሮች ጥቅም ላይ ሊያውሉት ? አብረን እንይ…
    መቼም የዚህ ፅሁፍ ተከታታዮች መፈንቅለ ድህነት ያልኩትን ታላቁን የኢትዮጵያ ታሪካዊ  የህዝብ ግድብ እንዳይፋጠን የሚያጓትቱ ምንጊዜም ቢሆን እጃቸውን ወደ ስርቆት እንጂ ወደ ልማት በማይሰዱ ልማደኛ የእጅ አመል ያለባቸው ሌባ አመራሮችን በአባይ ስም በመተቸቴ ከስርቆታቸው እንዲታቀቡ “ሳይቃጠል በቅጠል” ከስርቆታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ እና እየሰረቁ ያሉትን ለመጠቆም እንጂ ልማታችን የጋራችን ነው።
       በአባይ ግድብ ውስጥ ከሚገኙ ከ7 በላይ ድርጅቶች መካከል
1ኛ. ኣለማየሁ ኮንስትራክሽን የአቶ አለማየሁ ከተማ የግል ድርጅት፤
2ኛ .ገነት ኮንስትራክሽን የተሰኘውና በአቶ አብርሃም ለገሰ ስራ አስኪያጅነት የሚንቀሳቀስ የአቶ ሙሉጌታ የግል ድርጅት፤
3 ሮኮውን ኮንስትራክሽን የተሰኘው። ኢንቺሱ በተባለ ማናጀርና አቶ  እስቲፋኖስ የተባሉት ምክትል ስራ አስከያጅ ያሉበት፤
4. ጋድ ኮንስትራክሽን የእቶ ገዛሀኝ የግል ድርጅት ሲሆን በአቶ ታጠቅ ስራ አስከያጅነት የሚመራው፤
5ኛ.መከላከያ ኢንጂነሪንግ ባለ 24 ቢሊዮን ብር ስራ የያዙ ሲሆን
6ኛ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን  በኢንጂነር ቨርዴይ የሚመራ፤
7ኛ ሃኪኮ የጣሊያናዊቷ ሴት ኢንጂነር ኦርቺድ ድርጅት እና ሌሎችም ናቸው።
         በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት በርካታ ድርጅቶች  ውስጥ በአመራርነትና በስራ አስፈፃሚነት የተቀመጡት በግልፅና በድብቅ  በሚገርም ሁኔታ የህዝቡንና የሃገርን ሃብት እያጠፋፉት ያሉ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሰርጎ ገቦች፥ ዘረፋውና ስርቆቱን ረዥም ልምድ ያካበቱበት ስለሆኑ በቀላሉ ማነኛውም ኦዲተር የሂሳብ መዝገብ መርምሮ እጅ ከፍንጅ ሊያገኛቸው ባለመቻሉ እስካሁን ውስጥ ለውስጥ  እየተሽሎከሎኩ ራሳቸው የሰረቁትን ሌሎች የሰረቁ በማስመሰል “አይጥ በበላ  ዳዋ በዱላ” እንዲሉ ራሳቸው ወያኔዎች እንደፈለጋቸው በሚያሽከረክሩት ፅህፈት ቤት፥ መስሪያ ቤትና ቢሮዎች ውስጥ መረጃዎችንና ዶክመንታሪ መዝገቦችን በሚፈልጉት ሁኔታ በመሰረዝና በመደለዝ እስከሁን ድረስ ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ኪስ ለቅዱስ አላማ እየተጠራቀመ ያለውን ገንዘብና ማቴሪያል በመስረቅ ላይ ይገኛሉ።
      በእርግጥ የዘገየ ቢመስልም የሚቀድመው በሌለው ጌታ ፊት ፅዋቸው የሞላ በርካታ አደገኛ  ሌቦች እየተባረሩ ዘመናዊ የስርቆት ክህሎት ያላቸውና ለወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ባለስልጣናቶች ካዝና መሙላት የሚችሉ የማይነቃባቸው እየተተኩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል።- 
 1. የደህንነት ሃላፊ የነበረው ጀኔራል አሰፋ ከዚህ በፊት የጣና በለስ ፕሮጀክት ሲሰራ የንብረት ክፍል ሃላፊ ሆኖ፥ እጅግ ልዩ በሆነ ሁኔታ ብዛት ያለው ንብረትና ብር  ሲሰርቅ ከቆየ በኋላ  አሁን ደግሞ በአባይ ግድብ ውስጥ የደህንነት ክፍል ሃላፊ ሆኖ እያለ ለስራው ማፋጠኛ ከተለያዩ ሃገራት በውድ ገንዘብ እየተገዙ የገቡ ማሽኖች በተደጋጋሚ መጥፋታቸውን ተከትሎ የአሰፋን ተጠያቂነት  ያረጋገጠው ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በስውር እንዲቀየር ሊያደርገውና የመልቀቂያ ወረቀት ሊያሰራለት ኦዲተር ገብቶ በተደረገ ግርድፍ ማለትም ቀላል የሂሳብ መዝገብ ምርመራ  (ኦዲቲንግ)  35 ሚሊዮን  ብር ከሂሳብ ደብተሩ ተገኝቷል፣ ሆኖም ያለምንም ጥያቄ ወደ ሌላ መስሪያ ቤት እንዲዛወር በማድረግ ምክትል ሃላፊ የነበረው ኮማንደር ደሳለኝ የተሻለ የስርቆት ብቃት እንዳለው ታምኖበት እየሰረቀ ይገኛል።
2ኛ. ሌላው በወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የፍልስፍና ቀመር በተቀመረ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ስም የራሳቸውን ህዝብ ህይወትና ንብረት ለአረመኔው ወያኔ  የሚያስገድሉና የሚያዘርፍ፥ ብ.አዴ.ን ፥ደ.ህ.ዴ.ንና ኦ.ህ.ዴ.ድ የሚል ታርጋ ተፈልስፎ ከተለጠፈላቸው የጡት አባቶቹ መካከል ከኦ.ህ.ዴ.ድ የመጣው ኣቶ ማሙሽ በህዳሴ ግድብ ውስጥ የትራንስፖርቴሽን ክፍል ሃላፊ በነበረበት ሰዓት አሰራረቁና የዘረፋ ልምዱ ዘመናዊ ካለመሆኑ የተነሳ እንኳን የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.ን ካዝና ሊሞላ ይቅርና የራሱንም ኪስ መሙላት የማይችል ሞላጫ መሆኑን የተገነዘበው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መላ በመፍጠር ኦሮሞ በመሆኑ  ዘረኛ ነው የሌሎችን ብሄር ሰራተኞች ይጨቁናል በማለት ከገመገመ በኋላ ምክትል ሃላፊ በማድረግ እንዳያባርረው በአሰራራቸው የተቆጡ የኦሮሞ ተወላጆችን ተቃውሞ እንዳይስፋፋ በመስጋት እና እንዳይቀርብ አግዶ ዋና ሃላፊ ኣቶ ማሪኖ እርሱን ደግሞ ም/ሃላፊ ሆኖ ይገኛል።
3. ጃሉካ በመባል የሚጠራው የሃገር በቀል ድርጅቶችን በህዳሴ ግድብ ውስጥ ያሉትን  የሚቆጣጠር ሲሆን በአደረገው የሙስና ማግበስበስ በትንሹ ከ350 ሺህ ብር በላይ በመቀበልና በቀጥታ በየድርጅቶች ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የማስፈፀሚያ ብር ጠራርጎ በመብላት ወደ መጨረሻ አካባቢ ካዝናቸውን ባዶ ካስቀረ በኋላ በወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. የአሰራር ስልት ተባርሯል በሚል ተቀይሮ አሁን ደግሞ የተዋጣለት አጭበርባሪ አመሃ የተባለ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. የአብራክ ክፋይ እንዲቆጣጠር ተሹሟል።
4. ሌላው የጥበቃና የደህንነት አግልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው ህዳሴ ዲቪዥን በመባል የሚጠራው የፌድራል ፖሊስ ዋና አዛዥ ሆኖ የሚሰራው ኮማንደር ኪሮስ የተባለው የወያኔ ኢህ.አዴግ አስኳል ለተለያዩ ስራዎች ከጃፓንና  ቻይና የገቡ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ሁለት ማሽኖች ተበላሽተዋል እንዲባሉና የበታች አባሎቻቸው እንዲጠብቁት ከተደረገ በኋላ በሌሊት ያለምንም ከልካይ የወያኔው ኮማንደር ኪሮስ አውጥቶ እንደወሰደውና እንደሸጠው ከዚያም በድብስብስ እንደቀረ ማንም የሚመሰክረው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። አሁንም ከኮማንደሮች ወደ ኮማንደሮች እኩይ ተግባር ስናልፍ።-
  5. ኮማንደር አበበ በህዳሴ ዲቪዥን ውስጥ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል አዛዥ ሲሆን መጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ  ከሳሊኒ ኮንስትራክሽን  ድርጅት በቢሊዮን ብር በሚገመት የተገዙ ጀኔሬተሮች ሰርቆ  በመኪና በመጫን አድራሻውን በማጥፋት ከተሰወረ በኋላ “የሌባ ዓይነ ደረቅ” እንደሚባለው መጋቢት 19 ቀን 2005 ዓ/ም 7 ከሳሊኒ የጥበቃ ሰራተኞችን ማለትም 5ቱን በዋናነትና  2ቱን በተጠርጣሪነት አስሮ እየገረፈ ካቆየ በኋላ መጋቢት 20 ቀን 2005 ዓ/ም በራሱ መኪና በመጫን ምንም የማያውቁ ምስኪን የጥበቃ ሰራተኞችን አሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀርባለሁ በማለት የወሰዳቸው ሲሆን በረሃ ላይ ይግደላቸው፥ ፍርድ ቤት ያቅርባቸው፥ ከስራ ተባርረዋል ስለተባለ የታወቀ ምንጭ አልነበረም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተሰረቀውን ከባድ ጀነሬተር የጫነው መኪና ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በመተከልና በአዊ ዞን መካከል ቻግኒ ከተማ ለመግባት በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ካር ተራራ ስር የሚጠብቁ የኬላ ሰራተኞች አስቁመው ሲጠይቁት የተበላሸ ስለሆነ ወደ ጥገና እየወሰድን ነው ከሚል ማስተባበያ ቃል ጋር የኮማንደርነት ማዕረጉን የሚገልፅ መታወቂያ በማሳየት ያለምንም ጥያቄና ፍተሻ በማለፍ ሽጦት እንደተመለሰ በመረጃ ተረጋግጦ እያለ  አሁንም በነበረበት ስራ ላይ እንደሚገኝ እየገለፅሁ ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንቆቅልሽ እየተጫወተ ፍርድ ቤቶችን በድን ወና ማድረጉ ሰውን ሳይሆን እንስሳትም ያስደንቃል።
      ከሁሉም በላይ በሚገርም ሁኔታ የስርቆት ልምድና ተሞክሮ ያላቸው የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባላት ኮማንደር አበበና ጓደኞቹ “የሰማ ሌባ በተኛ ይቀባ” እንደሚሉት ብሂል አበው የቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው ኮማንደር ደሳለኝ በህዳሴ ግድብ ውስጥ የሴኪውሪቲ ማኔጀር ሆኖ እየሰራ ሳለ ባደረገው ከመጠን በላይ የሆነ የሙስና ማግበስበስ “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል”እንዲሉ ሁሉ የአሰራረቅ ዘዴው በግላጭና ፋራነትን የተላበሰ በመሆኑ መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ/ም በሌባው ኢ.ህ.አ.ዴግ የማዘዋወሪያ ስልት በተደረገለት ግምገማ በሚሊዮኖች የሚገለፅ ገንዘብ በመዝረፉ ተባርሯል በሚል ዝውውር እንደተደረገለት ያልተረዳው ኮማንደር አበበ ኮማንደር ደስለኝን ከ5 ወጣቶች ጋር በመሆን የሳሊኒን ዋናውን ጀነሬተር ሰርቆ ሸጠው ሲል መደመጡ ምን ያህል እርስ በርሳቸው እንደማይናበቡ ማወቅና መረዳት ይቻላል።
     6 ኮማንደር የማነ ይባላል የህዳሴ ዲቪዥን የፌዴራል ፖሊሶች የሻለቃ ሶስት አዛዥ ነው፣ የዚህ ደግሞ ልዩ ተዓምራዊ ዘዴው የሲኒየር መንስ ቤት ማናጀር ሆኖ የሚሰራውን አቶ ተመስገን ከተባለው ጋር ሽርክና በመፍጠር 400ሺህ ብር የሆቴሉን ጠቅላላ ካፒታል ከተከፋፈሉ በኋላ አቶ ተመስገንን ወደ መሃል ሃገር ሸኝቶ ካራቀ በኋላ የጠፋውን ገንዘብ ደግሞ ተመስገን ሁሉንም የሰረቀ በማስመሰል ራሱን ነፃ አድርጎ በቦታው እስከአሁን መኖሩን መናገሬ አባይን እንዳይገደብ መከልከል ያስመስልብኝ ይሆን?
    7. ኮማንደር አብረሃ አባይ ውስጥ  የምዕራብ ዲቪዥን የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ አቶ ዋሲሁን ከተባለው የሳሊኒ ዋና አስተዳደር ክፍል የነበረ ጋር በመሆን በመጀመሪያ ወደ ድርጅቱ ቅጥር የሚጠይቁ ሰራተኞችን የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ካልሆናችሁ አንቀጥርም በማለት ጉቦ እንዲከፍሉ በማድረግና የክፍያ ሁኔታውን በተመለከተ እየሰሩ በስውር እንዲከፍሉ በማድረግ 124 ሺ ብር ተቀብለዋል። በዋናነት ግን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ብዛት ያለው የእርሻ መሬት በሚሊዮናት በሚቆጠር ብር ከሸጠ በኋላ አቶ ዋሲሁን እንደሚፈለግ ሲያውቅ አሳልፎ እንደሰደደውና ሰርቆ ጠፋ በማለት የይፈለጋል መልዕክት እንዲሰራጭ ማድረጉን ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያውቅልኝ ለህዳሴ ግድብ መቃወም አይሆንብኝም።
    8 ኮማንደር ብርሃኔ ይባላል የህዳሴ ዲቪዥን የሻለቃ ሁለት(2) ዋና አዛዥ ነው በግድቡ ስራ ላይ በቀን ሰራተኛነት የምትተዳደር ወጣት ገነት የተባለች ሰራተኛ በኢጣሊያዊ ሳሊኒ ኩባንያ ቅርንጫፍ ስር በሚስተር አርዳይ የሚተዳደረው ሚስተር ኦርጋ የተባለው የኮንስትራክሽን ባለሙያ ወጣቷን ህዳር 18 ቀን  2005 ዓ/ም  ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ክብረ-ንፅህናዋን ይደፍራትና ሌሊቱን በሙሉ ሲጫወትባት ያድራል። ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ያወቁ ጓደኞቿ በቀጥታ ሰው መስሎኣቸው ለኮማንደር ብርሃኔ በዝርዝር ያስረዱታል ሆኖም ግን ኮማንደሩ ወጣቷን ሚስተር ኦርጋ እንደደፈራት በመረጃ ካረጋገጠ በኋላ ለገነት በግሏ እዚህ ውስጥ የሚሰሩ ከውጭ ሃገር የመጡ ሰራተኞችን ማናገር ክልክል ነው ራስሽን መጠበቅ ነበረብሽ ብሎ በማስፈራራት ለትራንስፖርት ከኪሱ አውጥቶ በመስጠት ባስቸኳይ ወደ መሃል አገር እንድትሄድ ካደረገ በኋላ ሚስተር ኦርጋ የተባለውን ሰራተኛ በመረጃው መሰረት የአስገድዶ መድፈሩ ወንጀል በእስራት ከ 8 ዓመት በላይ እንደሚታሰርና በገንዘብ ደግሞ ከፍተኛ ብር እንደሚቀጣ ከነገረው በኋላ ሁሉንም ነገር ለማምከን ግን ከእርሱ ጋር መደራደርና መስማማት እንዲችል አድርጎ ካሳመነው ብኋላ ሚስተር ኦርጋ ሊከፍለው የሚችል ጥሬ ገንዘብ ስላልነበረው ውድ የሆኑ የግንባታ እቃዎች አውጥቶ እንዲሸጥ በማድረግ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ እቃዎች ተዘርፈው ሲሸጡ ገነት የተባለችው ሰራተኛ ደግሞ ስራ ለቅቃ ስለነበር በእርሷ ስም ለግል ጥቅሙ አውሎት የተገኘ መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ።
እነዚህ ከውስጥ የሚከናወኑ ሲሆን በቅርቡ ጥር 7ቀን 2006 ዓ/ም ለአባይ ግድብ መስሪያ ተብሎ በታርጋ ቁጥር ኮድ 3-66303 አ.አ የሆነ መኪና ጭኖ ሲሄድ የነበረ ቴዲኖ ጣውላ አካፋ እና ሌሎችም የህንፃ መሳሪያዎች በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ አቶ ፍቅሩ አሰፋ ለተባለ ነጋዴ ተሽጦ ሲራገፍ በወዛደሮችና በ ነጋዴው  መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በመጡ ፖሊሶች ሊያዝ ሲችል ባለመኪናው መኪናውን አቁሞ መጥፋቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልማት ማሰብ ይሆን?
   ለማንኛውም ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ምርጥ ፈላስፋ የተዋጣለት ዘዴኛ ነው ግን ምን ያደርጋል ለጥፋት፥ ለስርቆትና ለዘረፋ እንጂ ለልማት ስለማይጠቀመው አባይን ገድቦ ነገ ምን ሊያደርግ ይችላል? አብረን እናያለን።
      
ይቀጥላል…