Sunday, September 28, 2014

መስከረም 6/2007 ዓ.ም የህወሃት ባለስልጣኖች በክልል ደረጃ ለሃይማኖት ሓላፊዎች በመቀሌ ከተማ ሰብስበው ህዝቡ በመጭው ምርጫ ህወሃት ኢህአዴግን ካልመረጠ ሃይማኖታዊ ግጭት ይነሳል በማለት ቅስቀሳ ላይ እንደሰነበቱ ለማወቅ ተችሏል።



   የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው የህወሃት ባለስልጣኖች በአስቸኳይ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ሰብሰባ በመጥራት በመቀሌ ከተማ እያካሄዱት ያለው ስብሰባ በ2007 ዓ/ም ህወሃት ኢህአዴግ ለሚያካሄደው ምርጫ ሁሉም አብያተ ክርስትያናት ለኢህአዴግ ድርጅት እንዲመርጡ ለማድረግ የራሳቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸውና የሆነ ቄስ በነፍስ አባትነት ለያዘው ነፍስ ወከፍ ሰው ለኢህአዴግ እንዲመርጥ ለማድረግ የተቻላቸውን ያህል ቅስቀሳ እንዲያደርጉ አስገዳጅ ትዕዛዝ እንደወረደላቸው ምንጮቻችን ገለፁ።
   ሲካሄድ የሰነበተው ስብሰባ በህወሃት የፖለቲካ ፅህፈት ቤት ሓላፊ አቶ ቴወድሮስ ሓጎስ የሚመራ ሲሆን እሱ እንደሚለውም ህዝብ እኛን ካልመረጠ በሃይማኖቶች መካከል ከባድ የሆነ ግጭት እንደሚፈጠር በመግለፅ በሚካሄደው ምርጫ የግድ ህዝቡ ለወያኔ እንዲመርጥ የአብያተ-ክርስትያን መሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገኛችሁ ቅስቀሳ አድርጉ የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ቷውቋል።
  እንደመረጃው አገላለፅ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ ገዥው መደብ ፖለቲካ በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ብሎ በህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውን ወደ ጎን በመተው አሁን በሃይማኖት በኩል አድርጎ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ እንዲካሄድ መመሪያ ማውረዱ  ስርዓቱ ምን ያህል በተበላሸ መስመር ላይ እየሄደ እንዳለ የሚያሳይ እኩይ ተግባር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።