Tuesday, September 29, 2015

በደቡብ ክልል በጌዲዮ ዞን ከድርቅ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ረሃብ ተከትሎ በርካታ ዜጎች ወደ ከተማ እየፈለሱ ሲሆን፣ እርዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው ጎዳና ላይ ማደር መጀመራቸውን የተለያዩ ምንጮች ገልጸዋል።



መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያሰማሯቸው ባለሙያዎች በዞኑ 80 ሺ ህዝብ መራቡን ሪፖርት ሲያደርጉ፣ የዞኑ የመንግስት ባለስልጣናት በተቀራኒው በዞናቸው ምንም የተራበ ሰው የለም የሚል  የሃሰት ሪፖርት አቅርበዋል።
ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በድብቅ በየቤቱ እየዞሩ በረሃብ ምክንያት ተኝተው ያገኟቸውን ሰዎች ፎቶ እያነሱ ለመንግስት ባለስልጣናት ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ በድጋሜ ማጣራት እንዲደረግ ተብሎ መመሪያ ሲወርድላቸው፣ በዞናቸው 4 ሺ ሰዎች ብቻ በረሃብ መጠቃታቸውን ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በባለስልጣናቱ በመበሳጨት ” የራሳችን ልጆች የሆኑት ባለስልጣናት እየበሉን ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፣
በዋና ዋና ከተሞች በብዛት ህፃናትና ወጣቶች ጎዳና ላይ እየወጡ ሲሆን፣ የሚለምኑና የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚፈልገው ህዝብ ቁጥር ባለፈው ታህሳስ ወር ከተገለጸው አሃዝ መብለጡን አስታውቋል። ቀድም ብሎ 4 ሚሊዮን 500 ሺ ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ድርጅቱ የገለጸ ቢሆንም፣ ተጨማሪ 400 ሺ ህዝብ የምግብ እርዳታ እየተደረገለት ነው ብሎአል። በተለያዩ ክልሎች ረሃቡ እየተባባሰ በመምጣቱ አፋጣኝ መልስ እንደሚያሻ ድርጅቱ አስታውቋል።