Thursday, January 26, 2017

ከውድቀት ለመዳን የተመረጠ የወያኔ ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ምህዳር፣ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ሲለቀቅ የሰነበተውና ያለው የሰላማዊ ትግል ጉዳይ ወያኔ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋርና ሌሎች የአገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ጋር በሩን ከፍቶ የመደራደሪያ ሂደት አዘጋጅቶ እንዳለ እየገለፀ ይገኛል።
ይህ የኢህአዴግን ባህርይና ተግባር የማያውቅ የለም እንኳ ብንልም ምናልባት ራሱ ባደራጃቸው ፍሬ የሌላቸው አንዳንድ ተቃዋሚ ነን ባዮች ሚዲያ ላይ ቀርበው አፋኝ ተግባሩን ረስተው ወያኔ ኢህአዴግ የዴሞክራሲያዊ አሰራሩን በር አስተካክሎ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳመጣ አድርጎ እንዲገልፁ የሚደረገውን ግን ልንነቃባቸው ይገባል።
የስርዓቱ ካድሬዎችም ወያኔ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሚስማማበት አብሮ ሊሰራ፣ በሚለያይባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ህዝብ የሚከታተለው የክርክር መድረክ አዘጋጅቶ እንዳለ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲፈርሙት የቆዩት የሥነ ምግባር ደንብ እንደተረፈና ለዚህ የሚቆጣጠር ፅ/ቤት ደግሞ እንደተቋቋመ ገልጸዋል።
ይህ በአንድ በኩል እየተከተለው የነበረውን ቀያጅና አራጊ ፈጣሪ አሰራሩንና ተግባሮቹን ስህተቱን እየነገረ እንኳ ቢሆን አሁንም ከፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራቱና ፀረ ህዝብ ድርጊቱ ታርሞ ወደፊት ሊያራምደው የሚችል ምቹ ቦታና የተለያዩ አመለካከቶችና ሃሳቦች በእኩል የሚያንሸራሽርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
ለምን ቢሉ ወያኔ ኢህአዴግ ውጥረት ውስጥ በገባበት ወቅት የሚፈጥራቸው በመሬት የማይተገበሩ መደበቂያዎች ወደ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ እስካሁን ሲንገራቸው የቆየና ያለው ጥሩ መሳይ ሃሳቦች ምን ላይ ዋሉ ብሎ ማስታወስ ያስፈልገናል።
እንዲያው ወያኔ ኢህአዴግ ከማንኛውም ጋር በአገሪቱና በህዝቡ ሁኔታና ያገባኛል ከሚል አካል ጋር ተደራድሮ ሊሰራ ከሆነ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታዊ አስተዳደር ብልሹነቱ በሱ ልክ እየተስፋፋ ያለው የፍትህና የህዝባዊ ወገንተኝነት እጦት የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት አስመልክተው ስለፃፉ ስለተቃወሙ አይደለም ወይ በየእስር ቤቱ እየታጎሩ ያሉ?
ከዚህ በዘለለ ደግሞ ዜጎች ለአመታት በላያቸው ላይ ሲፈፀም የቆየና እየተፈፀሙ ያሉት ግፎችና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት በሰላማዊ ትግል በኩል መፍትሄ አጥተው ትግስታቸውን እስከሚጨርሱ ታግሰው አማራጭ በማጣታቸው ምክንያት ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ሲሉ አይደለም ወይ ሳይወዱ በግድ ወደ አመፅ የገቡት?
እንደዚህ አይነቱ የወለደው ደግሞ በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላማዊ ትግል በኩል የወያኔ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ቦታ እንደሌለው አረጋግጧል። ምክንያቱም እነዚህ ተሳታፊዎች ህዝባዊ ተቀባይነት የነበራቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮችና አባላት በተለያየ መንገድ ሲበተኑ፤ ሲታሰሩ፤ ሲዳከሙ በዚህ ልክ ደግሞ ህዝባዊ ድጋፍ ሊያገኝ በማይችልበት ደረጃ ደርሰው እያየና እየታዘበ ነው።
ታዲያ ወያኔ ኢህአዴግ ከየትኞቹ ብቃት ያላቸው የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ተሟግቶ ነው አገርና ህዝብን ሊያድን የሚችል ሃሳብ አፍልቆ ህዝብ ከሚሻለውን አካል ሊደግፍና ሊቃወም የሚችል?
ካልሆነ ልክ እንደ አንዳንዶቹ በምርጫ ወቅት በተቃዋሚዎች ስም ያላችሁን አላማና ፖሊሲ ግለፁ ተብለው በግዜ ጥበት ምክንያት የያዙትን አማራጭ ፖሊሲና ሃሳብ ለህዝብ ሳያሳውቁ ይበቃችኋል ተብለው እንዲነጠቁ ማድረግና ሳይወዱ ደግሞ ለመንግስት ሲሳደቡና ከዚህ አልፎ የገዥው ፓርቲ የተወከሉ ካድሬዎች በተመደበላቸው በቂ ጊዜ የፈለጉትን አላማ ካሰረፁ በኋላ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሲያናንቋቸው አማራጭ ፖሊሲ የሌላቸው እየተባሉ ህዝብን ከስርዓቱ ጋር ለማስጠጋት ሲደረግ የነበረው አሰራር ለመድገም ነው የተፈለገው?
ለዚህ ሁሉ ፍትህና ዴሞክራሲ ለውጥ ፈላጊ የሆነ አካል እንዲያስብበት አስቦም መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል። ያለዚያ የወያኔ ኢህአዴግ መሪዎች ዴሞክራሲያዊ መብቴ ተጣሰ ብሎ መንግስትን የተቃወመ ዜጋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ደንግጎ በወገኖቻችን ላይ ከባድ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች እያወረደ ባለበት ወቅት ዴሞክራሲ ሊሰፍን አይችልም።

No comments:

Post a Comment