Wednesday, January 24, 2018

በአንድ ፍፃሜ ሁለት ውሣኔ



    በአሁኑ ወቅት የአገራችን ህዝቦች ከከፋ ወደ ባሰ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛሉ ብቻ ሳይሆን በስጋትና ውጥረት ውስጥ ተቀርቅረው ይገኛሉ። 
    ይህ ደግሞ አገሪቱን ወክሎ ህዝብ እመራለሁ እያለ አገርን መሬት ላይ በሌለ እድገት እየመዘገበ፤ እራሱ ያደፈረሰውን የህዝቦች ውስጣዊ አንድነት ደግሞ ዋስትና ያለውና አንፀባራቂ ሰላም ሰፍኗል፤ ለግፋዊ ተግባራቱ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሰፍቷል፤ ለሚዲያ አፈናው የፕሬስና የሚዲያ ነፃነት ተረጋግጧል፤ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቱ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት ነግሷል፤ለህዝቦች ጥያቄና ተጠቃሚነት ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በማሳለጥ የህዝቦች ጥቅም ተረጋግጧል ወዘተ በሚሉ የተሰናበታቸው የ26 ዓመታት የማደናገር ጉዞ፣ ዛሬ ሁሉም ምክንያቶቹ ከሽፈው እራሱ ቡድኑ ባመጣው መንገድ ሊቀጥል በማይችልበት ደረጃ መድረሱ ብቻም ሳይሆን ሁሉ ስራዎቹ ተስተጓጉለው በገደል አፋፍ ስር ሆኖ እድል ስጡኝ ሲል ይውላል።
    ይሁን እንጂ የወያኔ ኢህአዴግ ቀደምት ተግባሮች አገራችን ኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ ዜጋ የማይታይ እድገት እያስመዘገበች ሚሊዮኖች በአስከፊ ድህነት ተዘፍቀው የሚኖሩባት ለጥቂቶች ደግሞ ምድረ ገነታቸው ለመሆን ያስቻላት ብልሹና ጨፍላቂ ስርዓት መሆኑን ሁሉ ስለነቃበት አሁን በሚያደርጋቸውና በሚሰጣቸው መግለጫዎቹ የሚደናገር የለም።
    ምክንያቱም የክህደትና የአፈና፤ የመርገጥና የሙሰኝነት ዓመታትን የአገራችን ህዝቦች በሙሉ በተለያዩ መንገዶችና አጋጣሚዎች ተጠቅመው በማያሻማ መንገድ ለዚህ የውሸት እድገት መሬት ላይ የለም፤ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት ተረጋግጧል የምትሉት፣ ህዝብ እየታሰረ፤ እየተንገላታ፤ እየተገደለ አድራሻው እየጠፋ ነው፤ ፍትህ የለም ልማትና መልካም አስተዳደር አልተረጋገጠም እያላቸው መጥቷል። እያላቸውም ይገኛል።
    ይሁን እንጂ የአገራችን ህዝቦች እውነተኛ ገፅታ እና የስርዓቱ አካሄድ በሚገባ ተቀብሎ ዘላቂ መፍትሄ ከሚያስቀምጥለት ይልቅ በጠላትነት እየተመለከተ አስተዳደሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያጠበውና በሁሉም መልክ ፀረ ህዝብ ተግባሮች እየፈፀመ ቆይቷል። አሁንም እየፈፀመ ይገኛል።
    በዚሁ ልክ ደግሞ የአገራችን ህዝቦችም በላያቸው ላይ እየደረሰ ያለውን  የወያኔ ኢህአዴግ ጭቆናና ረገጣ አነጣጥረው በመነሳት እያርበተበቱት ቢመጡም የተወሃደና የተደራጀ ሃይል ባለመኖሩ የተነሳ የሚነሳውን የህዝብ ተቃውሞ ለጊዜው በሃይል ሲበትነው ብሎም ከአንድ መድረክ ወደ ሌላ ተመሳሳይ መድረክ ሊያሸጋግረው የሚችል ቃልና ተስፋዎች እየገባ ባለማቋረጥ በደሎችን ለመፈፀም ችሏል።  
    በአሁኑ ወቅት ደግሞ መንግስታዊ ስራውን ትቶ እርስ በርሱ ለመበላላት በደረሰበት ደረጃ ሲሄዳቸው የቆያቸውን አውዳሚ ተግባሮቹ በማመንና ያለምንም ወንጀል መብታቸውን በመጠየቃቸው ሐሰተኛ ክስ ተመስርቶባቸው ከየአውራ ጎዳናው እየተለቀሙ ወደ እስር ቤት ያጎራቸውን በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ወገኖች ለተወሰኑት ለመፍታትና በምህረት ለመልቀቅ ብሎም የደርግ የነበርውን የሰው ማረጃ ህንፃ ዛሬ ዘግቼ ሙዚየም አደርገዋለሁ በሚል ማደናገርያ ለመወሽከት ተገዷል። 
    ከዚህ በተለየ ደግሞ ስንሄደው የቆየነው የሐሰትና የማደናገር ጉዞ ወጥተን የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት እናረጋግጣለን እያለ ባለበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት ጅምላዊ እልቂት ተፈፀመ በማለት የቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የሐዘን መግለጫ ሰጥቶ ነበር። 
    ከሣምንት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ደግሞ የስርዓቱ  የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሰጠው መግለጫ ይህንን የሚያጣራ ቡድን ተሰማርቷል በበኩሌ ጅምላዊ እልቂት ለማለት አልደፍርም ሲል ታይቷል። ታዲያ ይህ በአንድ ፍፃሜ ሁለት ውሣኔ እየሰጡ እንዴት ያለ ድርጊት ነው ችግር የሚያስወግድ ሃላፊነትና ችሎታ ያላቸው?
    ለማጠቃለል ይህ ቡድን ህዝብንና አገርን ሊያስተዳድር የሚችልበት አቋም አጥቶ ባለበት ወቅት በየጊዜው ሲሸፍናቸው የቆየ እኩይ ተግባራቱና ፀረ ህዝብ አስተዳደሩ በአንድ ፍፃሜ ሁለት እርስ በርሱ በሚጋጭ ውሳኔ የሚታለል ህዝብ እንደሌለ እያወቁ፣ ባለቀ ሰዓት ጊዜያችሁን አታባክኑ ተብለው ሊወገዱ ይገባል።

No comments:

Post a Comment