መንግስት የህግ የበላይነትን ባለማክበር ፤ በህገ-መንግስቱ የሰፈሩትን ሰብአዊ መሰረታዊ መብቶችን በመሸራረፍና
ለራሱ በሚያመቸው መንገድ በመተርጎም እየተከተለው ያለውን ጸረ-ዴሞክራሲና ጸረ-ህዝብ አካሄድ ምክንያት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ
ድጋፉን ነፍጎታል ፣በአሁኑ ግዜ በህዝቡ ውስጥ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ወደ ትግራይ ፤ ዓፋር ፤ አማራና ሌሎች
ለስርዓቱ ስጋታ ናቸው ወደ እሚባሉ በርካታ አከባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ማሰማራቱን ከቦታው የደረሰን ዘገባ
ያመለክታል ፣
በደረሰን ዘገባ መሰረት እንዲህ አይነቱ ካሁን ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት
ስምሪትና ሰራዊቱ ከነ ሙሉ ትጥቁ በከተማና ህዝብ በብዛት በሚገኙባቸው አከባቢዎች በሚያደርገው ያልተለመደ እንቅስቃሴ ምክንያት የአከባቢው
ኗሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል፣ ኗሪዎቹ ባደረባቸው ጭንቀት ከቤታቸው አርፍደው ስለሚወጡና ቀደም ብለውም ስለሚገቡ የዘወትር ስራቸውን
በአግባቡ መስራት አልቻሉም በዚህም ምክንያት ህይወታቸውን በተለመደው መንገድ ለመምራት ተቸግረዋል፣
ቀደም ሲል በአፋር ክልል ፤ በሎግያ ከተማ ፤ አባሃና በተባለ ሆቴል ውስጥ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊትና
የፈዴራል ፖሊስ አዛዦች ሲቪል ልብስ ለብሰው ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው ፣