Thursday, November 29, 2012

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ትህዴን) ከጭቆና ነጻ ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ የትጥቅ ትግል መሆኑን አምኖ እያካሄደው ያለውን ፈጣን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የኢህአዴግን ስርዓት ጭንቀት ውስጥ ከቶታል ሲል የድርጅቱ ሊቀ መንበር ታጋይ ሞላ አስገዶም ገለጸ፣፣







ታጋይ ሞላ ከኢሳት(ESAT)ሬድዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የትህዴን በብሄር ተደራጅቶ መታገል ስልታዊ መሆኑን ጠቅሶ ድርጅቱ ከተመሰረተበት ዕለት ጀምሮ ሃገራዊ ራኢ ያለው ፤ ግልጽ የሆነ ዓላማና ፕሮግራም ቀርፆ፤ በህዝቦቿ አንድነትና እኩልነት የተመሰረተች አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የተነሳሳ ለመሆኑ ድርጅቱ የሚከተለው የፖለቲካ መስመር በግልጽና በማያሻማ መንገድ ያመለክታል በማለት፤ ምንም እንኳ ትህዴን በትግራይ ተወላጆች የተመሰረተ ቢሆንም በውስጡ ያቀፈው የሰው ሃይል የመላው ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን ያካተተ ስለሆነ በይዘቱ ህብረብሄራዊ ድርጅት ነው ሲል አስረዱቷል።።
በመቀጠልም ታጋይ ሞላ በጣት የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በስልጣን ላይ ስላሉ ብቻ መላውን የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ አድርጎ መውሰድና በተለያዩ መንገዶች ለማስተጋባት መሞከር መሰረታዊ ስህተት መሆኑን ጠቅሶ እንዲህ አይነቱ አመለካከት የኢህአደግን የስልጣን እድሜ ከማራዘም ያለፈ ሌላ ፋይዳ እንደማይኖረው፤የትግራይ ህዝብ በተጨባጭ በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ብሄሮች ሁሉ የሚደርስባቸውን በደልና ግፍ ስለሚደርስበትና የኢህአደግ ካድሬዎች በሚነዙት የከፋፍለህ ግዛ ርካሽ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ በመሆን ፤ ወንድሞቹ ከሆኑት ሌሎች ብሄር ብሄረሰብች መነጠል ስለማይገባው እያካሄድነው ያለን የትጥቅ ትግል አንዱ ዓላማ የዚህ ዓይነቱ በተለያዩ ቡድኖች በተለያየ መልኩ የሚገለጽ የተሳሳተ ግንዛቤ ለማረም ጭምር መሆኑን አስገንዝቧል።።
በገዥው መንግስት ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚዎች በስልጣን ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ብቻ አድርጎ ማቅረብም ስህተት መሆኑና በዚህ ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚዎቹ ሁሉም ስርዓቱን አምነው ተቀብለው በስልጣን ላይ የሚገኙ የሌሎች ክልሎችና ብሄሮች ተወላጆች ጭምር መሆኑ ላፍታም ቢሆን ሊዘነጋ የማይገባ ሃቅ ነው በማለት ፤ተጨባጭ ሃቁ ይህ እያለ ከጭቁን ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለ 17 ዓመታት ሙሉ ደምቶ ፤ አካሉ ጎድሎና ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ኢትዮጵያን ከፋሽሽቱ የደርግ ስርዓት መንጋጋ ውስጥ ፈልቅቆ ያስወጣ የትግራይን ህዝብ ብቻ በመነጠል ሳይጠቀም ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ሲል ታጋይ ሞላ ጨምሮ ገልጸዋል።።
በመጨረሻም ታጋይ ሞላ የትጥቅ ትግል ማለት በተወሰነ የግዜ ሰሌዳ ተቻኩለህ ድልን የምትቀዳጅበት ሂደት ባለመሆኑ ትህዴን ባሳለፋቸው 12 የትጥቅ ትግል ዓመታት ትግሉ የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ እየከፈለ በርካታ መሰናክሎችንና ፈተናዎችን በማለፍ በአሁኑ ግዜ በሚያስተማምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፤ በአንጻሩ የኢህአደግ ስርዓት እየተሰነጣጠቀ መሆኑንና ክፍተቱንም መጠገን በማይችልበት ደረጃ መድረሱን አመልክቶ ፤ በኢትዮጵያዊያን ጥምረት ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ (ኢጥድለ) ስር ተደራጅተን የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የምንገኝ ድርጅቶች ሳንዘናጋ የጀመርነውን ጥምረት ይበልጥ አጠናክረን እንድንቀጥልበት ሌሎች በዚሁ ጥምረት ያልታቀፉ የትጥቅ ትግል የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመሬት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ድርጅቶችም አሁኑኑ ወደ ጥምረቱ እንዲቀላቀሉ ጥሪ በማቅረብ ፤ እጅና ጓንት ሆነን በህብረት በመታገል አምባገነኑ የኢህአደግ መንግስትን የምናስወግድበት ወቅት አሁን ነው ሲል አስምረቦቷል።