በሰ/ምዕራብ ትግራይ የሽረ-እንዳስላሰ ከተማ መስተዳድር በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ያልተደራጀ ኗሪ እንደ
ስኳርና ዘይት የመሳሰሉ በመንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው የሚቀርቡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ተጠቃሚ አይሆንም የሚል ውሳኔ
በማሳለፉ ምክንያት የከተማዋ ኗሪ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ካለፍላጎቱ እንዲደራጅና የድርጅት የአባልነት መውጮም 12 ብር እንዲያዋጣ
እየተገደደ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በአከባቢው ኗሪ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ የመጣው ህወሓት-ኢህአዴግ ህዝቡን በጉልበት
ለመቆጣጠር ሲል ገበያን ለማረጋጋት በሚል ሽፋን በመንግስት የሚቀርቡትን መሰረታዊ የፍጆታ ሽቀጦችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ኗሪው
የግድ የህወሓት አባል እንዲሆንና ድርጅታዊ መዋጮም በመክፈል የህወሓት አባል ነኝ ብሎ ያለውዴታው እንዲፈርም እያስገደዱት መሆኑን
የደረሰን ዘገባ ያስረዳል።
የከተማዋ
ኗሪ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት 17 ዓመታት ሙሉ የደርግን ስርዓት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ
ትግል የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ህወሓትን ወደ ስልጣን ለማብቃት ጉልህ ድርሻ ከተጫወቱት አንዱ ቢሆንም በአሁኑ ግዜ ህዝቡ መብቱ
እንዲጠበቅለት በመጠየቁ ብቻ በአምባገነኑ የህወሓት-ኢህአዴግ ስርዓት የተለያዩ ሰሞች እየተሰጡት በከፋ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ
ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ በተለያየ ግዜ መዘገባችን የሚታወስ ነው ።