የትግራይ ህዝብ ከነበረው መደባዊና ብሄራዊ ጭቆና ለመላቀቅ በማሰብ የትጥቅ ትግሉን እንደመጨረሻ አማራጭ
አድርጎ በጠላቶቹ ላይ ሲያካሂደው የነበረው መራራ ትግል ለፍትህ፤ለእኩልነት፤ለዴሞክራሲና በላዩ ላይ የነበረውን ድህነት ከትክሻው
ላይ ለማውረድና የበለፀገች አገር ለመገንባት በማሰብ ነበር፣፣
የአገራችንን ስርአቶች በመቃወም እየተካሄዱ
የነበሩት ትግሎች መጠነ ሰፊ መስዋእትነት የተከፈለባቸው መሆኑ ቢታወቁም በተከፈለው መስዋእትነትና በደረሰው ጉዳት አንፃር ሲታይና።
የነበሩት ስርአቶች ከተገረሰሱ በኋላ እዚህ ግባ የሚባል መሰረታዊ ለውጥ አልመጣም ብቻ ሳይሆን የወደፊት ተስፋ የሚያሳዩ ምልክቶችም
ማየት አልተቻለም፣፣
የትእምት ድርጅቶች ለትግራይ ህዝብ ጥቅም
አልዋሉም በሚል ርእስ ማእከል ተደርጎ በህወሃት የፖሊት ቢሮ አባልና የትእምት ዳይሪክተር የሆነችው አዜብ መስፍን ባለፈው ሳምንት
የትእምት ድርጅትንና ሌሎች አዳዲስ ሊገነቡ የታቀዱ ፋብሪካዎች አስመልክታ የሰጠችው ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ህዝብ ያላት ንቀት የሚያሳይ
እንደሆነ በግልፅ የሚያመለክት ነው።
“መሰንበት ደጉ” እንደሚባለው የህወሓት
ካድሬዎችና ባለስልጣኖች በየአመቱ ህዝባችን ለማታለል የተስፋ ዳቦ እየቆረሱ፤ በተለይ በየግዜው ለሚያካሂዱት የይስሙላ ምርጫዎች ሊያካሂዱ
በሚቀራረቡበት ግዜና ሌሎች ለስርአታቸው እድሜ ሊያራዝሙ ይችላሉ ብለው በሚያምንባቸው ጉዳዮች ላይ ከመጀመርያውም ጀምረው እየተጠቀሙበት
መምጣታቸውና አሁንም በስፋት እየሰሩበት መሆናቸው የሚታወቅ ሃቅ ነው።
የስርአቱ የበላይ ካድሬ አዜብ መስፍን ባለፈው
ሳምንት የትእምት ድርጅቶች አሁን ያሉበት ደረጃና ለወደፊት ምን መሆን እንዳለባቸው አስመልክታ በተናገረች ግዜ። በተለይ በአዲግራት
ከተማ ውስጥ የሚገኘው አዲስ መድሃኒት ፋብሪካና፤ በአድዋ ከተማ የተገነባው አልመዳ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ
ኪሳራዎች እንዳጋጠማቸውና አሁንም በባንኮች እዳ ላይ እንደሚገኙ መግለፅዋ
ይታወቃል።
እነዚህ የትግራይ ህዝብ ንብረት እንደሆኑ
የሚነገርላቸው ፋብሪካዎች ነገር ግን ለወያኔ ባለስልጣናትና ካድሬወቻቸው ብቻ እየጠቀሙ የሚገኙ ድርጅቶች ያመጡት ለውጥ እንደሌለ
እየታወቀ ህዝቡ በችግር አለንጋ እየተገረፈ ባለበት ባሁኑ ግዜ በድርጅቶቹ እየተጠቀመ ተደርጎ በመወሰዱ ባገራችን ዜጎች የጥላቻ አይን
ላይ እንዲገባ አድርጎታል።
የትእምት ድርጅቶች ለበርካታ ኪሳራዎች እየተጋለጡ
የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው ከተባለ መልሱ አንድና አንድ ነው! ጥብቅ የሰራተኞች ክትትል በሌለበት፤ ቀጣይና ተከታታይ
የኦዲት ቁጥጥር ስራ በማይካሄድበት፤ ባጠቃላይ በባለቤትነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚያስተዳደር አካል ባለመኖሩ ምክንያት ከአንድ
ፋብሪካ ብቻ ከ 9 መቶ ሚልዮን ብር በላይ ኪሳራ ማጋጠሙ ምን ያህል በድርቶቹ ውስጥ የስርቆት ተግባር ተስፋፍቶ እንደሚገኝ የሚያስረዳ
ነው። ይህ ለ17 አመታት ገደማ በህወሃት አመራሮች እየተዘረፈ የቆየውን ከፍተኛ ንብረትና በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብም በተለይ ለድርጅቱ
መሪዎች ከተጠያቂነት የሚያድናቸው አይሆንም።
የህወሃት የበላይ አመራርና የትእምት
ዳይሪክተር አዜብ መስፍን የአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አሁንም ቢሆን ካለበት ችግር አልተላቀቀም፤ መፍትሄ እንዲደረግበትም በጥረት
ላይ እንገኛለን ብላ በተናገረችበትና ባጠቃላይ የትእምት ፋብሪካዎች በህወሃት አመራሮች እየተዘረፉ ባሉበት ወቅት አሁንም በትግራይ
ተጨማሪ የብረታብረት፤ የከሚካልና የመሳሰሉት ፋብሪካዎች ይገነባሉ ማለትዋ የማሌሊት አመራሮች ከዚህ በፊት በተገነቡ ፋብሪካዎች መርካት
ስላልቻሉ አሁንም ተጨማሪ የስርቆት ማእከል እንዲገነቡ ማሰባቸው። አላማው ለምን እንደሆነ በጣም ግልፅ ነው።
የትግራይ ህዝብ
ግን ከድርጅቶቹ ምንም አይነት እርባና እንዳላገኘ በሚገባ ስለሚያውቀው ይህ በወያኔና አጫፋሪዎቹ 2007 ዓ/ም ላይ ሊካሄድ የታሰበውን
የይስሙላ ምርጫ ግምት ውስጥ በማስገባት እያካሄዱት ያሉትን የማደናገሪያ ቅስቀሳዎች ቦታ እንደማይሰጠው የሚያጠራጥር አይደለም።
የትእምት ፋብሪካዎች እንደሆኑም ወያኔንና
ጋሻ ጃግሬዎቹ ከዙፋናቸው ሳይነቀሉና ህዝቡን የሚያገለግል እውነተኛ ስርአት ሳይረጋገጥ እነዚህ ድርጅቶች ለቀጣይም ቢሆን ኪሳራ ውስጥ
እንደሚገቡና ውድቀታቸው ገሃድ እንደሚሆን የሚያጠያይቅ አይደለም፣ ምክንያቱም- የህዝቡን አደራ ተቀብሎ የሚሰራ ባለቤት በታጣበትና
ግልፅነትና ተጠያቂነት በሌለበት ብልሹ አሰራር ላይ ሆኖ ትርፍ ማምጣት ከቶ ስለማይቻል።