Sunday, January 4, 2015

በዓዲ-ጎሹና አካባቢው የሚገኙ የገዢው ኢህአዴግ ስርአት የፀጥታ አካላት ወንጀል ያልፈፀሙ ሰዎችን ከትህዴን ጋር በመገናኘት ትብብር ታደርጋላችሁ በሚል ምክንያት አስረው እያሰቃዩዋቸው እንዳሉ ተገለፀ።



በምንጭቻችን መረጃ መሰረት በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን ቃፍታ ሑመራ ወረዳ የሚገኙ ለሆዳቸው ያደሩ ፖሊሶች ከዞኑና ከወረዳው ደህንነትና ካድሬዎች አባላት ጋር በመሆን የስርአቱ አባላት ያልሆኑ የዓዲ-ጎሹ ንፁሃን ወገኖችን የትጥቅ ትግል ከሚያካሂደው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጋር ተገናኝታችሁ ትብብር ታደርጋላችሁ በሚል የማጥቆር ወንጀል ያለፈርድ ቤት ትእዛዝ በሑመራ ከተማ በሚገኘው የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ አስረው እያሰቃይዋቸው መሆናቸውን ታወቀ።
   መረጃው ጨምሮ እንዳስረዳው ታህሳስ 13/ 2007 ዓ/ም ከታሰሩት ዜጎች ተኽላይ ንጉሰ፤ መዃንንት አለምሰገድ፤ ተወለ አረፋይነ፤ ሓዱሽና ሌሎችም የሚገኙባቸው ንፁሃን ሰዎች በልዩ ሁኔታ ታስረው የሚገኙ ሲሆን ቤተሰቦቻቸው ሊጠይቋቸው ሞክረው ሊፈቀድላቸው ባለመቻሉ ምክንያት እየተንገላቱ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
    በተመሳሳይ በላእላይ አድያቦ ወረዳ የዕጉብ ቀበሌ፤ ታብር አካባቢ ነዋሪዎች የሆኑ 3 ወንድማሞች አልጋ ግርማይ ውልየስ፤ አፈወርቅ ግርማይ ወልየስና በዲያቆን ቅጥያ ስም የሚታወቀው ወንድማቸው በትህዴን ድርጅት የተደራጃችሁ ናችሁ በሚል ምክንያት ፖሊስ አስሮ እያሰቃያቸው እንዳለና በኑፁሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለ ፀረ ህዝብ ተግባር በባሰ ሁኔታ በመቀጠል ላይ እንዳለም ባለፈው ሳምንት በዜና እወጃችን መግለፃችን ይታወሳል።