Tuesday, May 5, 2015

በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን አላማ የያዘ ፓምፕሌት በመበተኑ የተነሳ የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች እርስ በራሳቸው እንዲጠራጠሩ እንዳደረጋቸው ተገለጸ።



በዚህ ሳምንት በሸሬ እንዳስላሴ ከተማ፤ አክሱም፤ ዓዲ ግራት፤ ተምቤንና መቐለ  የትህዴን አላማ የሚገልፁና የኢትዮጵያ ህዝብ በገዢው የኢህአዴግ ስርአት ላይ ተቃውሞ እንዲያነሳ የሚቀሰቅሱ ፓምፕሌቶች በተደጋጋሚ እንደተበተኑ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ድርጊት ስጋት ላይ የወደቁት የህወሓት/ኢህአዴግ የበላይ አመራሮች ውስጣቸውን ለመፈተሸ በውቅሮ ክልተ አውላዕሎ ወረዳ የወረዳውን አስተዳዳሪዎችና የህወሓትን ካድሬዎች ስብሰባ ላይ ጠምደዋቸው እንደሰነበቱ ለማወቅ ተችሏል።
   የስብሰባው አጀንዳም ጠላት በውስጣችን እንደፍላጎታቸው ገብተው እየወጡ ሳለ ለምንድነው የማንከታተላቸው? ለመሆኑ የድርጅቱ ካድሬና ህዝቡ ከህወሓት ጎን አለ ወይ? የሚሉና ሌሎችም አጀንዳዎች እንደነበሩ ከስብሰባው ተሳታፊዎች የደረሰን መረጃ አስታወቀ።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ በስብሰባው የተገኙት ተሰብሳቢዎች በበኩላቸው ህዝቡ ከጎናችን አይደለም፤ በውስጣችንም ትህዴንን የሚያግዙና ፓምፕሌት በመበተን እጅ ያላቸው አስተዳዳሪዎች አይታጡም በማለት እንደገለፁና በዚህ መሰረትም በውስጣቸው ትርምስና ስጋት እንደተፈጠረ መረጃው ጨምሮ አስረድቷል።