Sunday, October 4, 2015

በአማራ ክልል በግንባታ ስራ የተሰማሩ ተቋራጮች በጤና ጥበቃ ቢሮውና በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች አሰራር መማረራቸውን ከስፍራው የሚገኙ ምንጮቻችን ገለፁ።



እንደምንጮቻችን ገለፃ በአማራ ክልል የሚገኙ የህንፃ ተቋራጮች በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ከባድ ማጭበርበር እያጋጣማቸው መሆኑን የገለፁ ሲሆን  የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ዓርብ መስከረም 7/2008 ዓ.ም በድንገት በጠራው የተቋራጮች ስብሰባ፣ በክልሉ የሚገነቡ የጤና ተቋማትን በመስራት ላይ ያሉ ተቋራጮች በሙሉ ሰብስቦ ፤የግንባታ ስራዎች በመጓተታቸው ምክንያት ከልዩ ልዩ ግብረ ሰናይ መንግስታት የተገኘ የዕርዳታ ገንዘብ በየጊዜው ተመላሽ መሆኑ ቢሮውን አሳስቦታ ብሏል ተቋራጮች በተቻላቸው ፍጥነት ግንባታቸውን በማጠናቀቅ በዕርዳታ የተገኘውን ገንዘብ ከመመለስ እንዲያድኑት ጠይቋል።
የክልሉ የጤና ጥበቃ ቢሮ የዘርፉ ሃላፊዎች ግንባታው እንዲፋጠን ቢጠይቁም፣ ከተቋራጮች የተገኘው ምላሽ አስደንጋጭ ነበር። በርካታ ተቋራጮች በለቅሶና በምሬት በጤና ቢሮው የደረሰባቸውን በደል በመግለጽ ለመጓተቱ ተጠያቂው ቢሮው መሆኑን ሲናገሩ ተሰምተዋል።
የጤና ጥበቃ ቢሮው በአብዛኛው ‹‹በጀት የለም!! ›› በማለት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ያመላለሳቸው ተቋራጮች በምሬት ሲናገሩ፤ ጤና ጥበቃ ቢሮው የሰሩበትን ገንዘብ በወቅቱ ባለመክፈሉ በተያዘው ጊዜ ስራውን ጨርሰው ለማስረከብ አልቻሉም በዚህም ምክንያት በየፕሮጀክቱ ለሚሰሩ ሰራተኞችና ሙያተኞች ከተገቢው በላይ ክፍያ ለመፈጸም መገደዳቸውን ገልጸው፤ የሚከፍሉት በማጣት ንብረታቸውን እሰከ መሸጥ መድረሳቸውን በለቅሶ ሲገልጹ ተስተውለዋል።