Sunday, March 23, 2014

በመቐለ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በጨረታ በማሸነፍ የገነቡት የመንገድ ንጣፍ ስራ በውላቸው መሰረት እንዳልተከፈሉ ከከተማው ያገኘነው መረጃ አስታወቀ።



     በመረጃው መሰረት በስራ አጥነት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉ የመቐለ ከተማ ወጣቶች ከችግሩ ለመላቀቅ ብለው በማህበር ተደራጅተው በድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማለት በወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ተወዳድረው ቢያሸንፉም የከተማው አስተዳዳሪዎች ግን ከውሉ በኋላ ባጀት ተጨርሰዋል በሚል ምክንያት ውሉን በማፍረስና በቅናሽ ዋጋ ተገደው እንዲሰሩ በማስገደድ ላይ እንደሆኑ ተገልፀዋል።
     ወጣቶቹ! ይህ በመቐለ ከተማ አስተዳዳሪዎች በላያቸው ላይ እየተፈፀመ ያለው ኢ-ፍትሃዊ አሰራር በጨረታው ውል መሰረት እንዲከፈላቸው ለሚመለከታቸው አካላት ቢጠይቁም። አጋጥሞ ላለው የስራ አጥነት ሁኔታ ተጠቅመው ካስፈለጋቹህ ስሩ ካላስፈለጋቹህ ተውት በማለት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሰሩና ባለስልጣናቱ የተመደበው በጀት ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት መሆናቸው ለማወቅ ተችለዋል።
     ይህ በእንዲህ እንዳለ በመቐለ ከተማ ቀዳማይ ወያኔ በተባለው ቦታ በወጣቶች የተሰራው የመንገድ ንጣፍ ስራ በመጋቢት 4/2006 ዓ.ም በዘነበው ዝናብ በመበላሸቱ ምክንያት በኪሳራ ላይ ኪሳራ እንደሆነባቸው የገለፀው መረጃው ለተበላሸው መንገድ ማስገንቢያ መሳርያዎች እንዲሰጣቸው በጠየቁበት ሰአትም ሰሚ ጀሮ ባለማግኘታቸው በራሳቸው ወጪ ዶዘር ተከራይተው እንደገና አስተካክሎው ለማስረከብ አቅም በማጣታቸው ምክንያት ማህበራቱ ስራውን ኣቛርጦው እንዲወጡ መገደዳቸው መረጃው ያመለክታል።
    እነዚህ በማህበራት ስር የተደራጁ ወጣቶች አስቀድመው   የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራውን ዝናብ ከመጀመሩ በፊት አስረክቡን ብሎው እየጠየቁ ቢቆዩም የመቐለ ከተማ አስተዳዳሪዎች ግን ዛሬ ነገ በማለት ስላዘገዩት ተጠያቂዎቹ ራሳቸው መሆን ይገባቸው በማለት ምሬታቸውን በመግለፅ ላይ መሆናቸው መረጃው አክሎ አስረድተዋል።