Sunday, April 13, 2014

የሸራሮ ከተማ አስተዳዳሪዎች በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን በመሰብሰብ መንግስት ሊያስተባብራችሁ ስለተነሳ ተደራጁ እያሉ በተናገሩበት ሰአት ተሰብሳቢዎቹ የማይተገበር የውዥንብር ቃል ነው በማለት መልእክቱን እንዳልተቀበሉት ተገለፀ።



በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን ሸራሮ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች ከተለያየ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮለጆች ተመርቀው ስራ ባለማግኘታቸው ምክንያት ባልተፈለገ ቦታዎች እንዲውሉ እየተገደዱ ባሉበት በአሁኑ ግዜ የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ለወጣቶቹ የሚያስቡ ለመምሰል መጋቢት 23/2006 ዓ/ም በመሰብሰብ አስተዳደሩ በሚፈልገው መንገድ ከተደራጃችሁ የፈለጋችሁትን ብድር እንድትሰጡና ለመስኖ፤ ለከብቶች ማደለብያ፤ ለደሮ ማራቢያ፤ ለብሉኬትና ሌሎችንም ለማምረት የሚያመች ሰፊ መሬት እንሰጣቹኃለን በማለት የማይተገበር ቃል እንደገቡላቸው ከቦታው የተገኘው መረጃ አስታወቀ።
የጥቃቅና አንስተኛ የንግድ ድርጅት ሃላፊ የሆነው መ/ር ተክሊት፤ የወጣቶች ሃላፊ ሃለቃ አመሃና አቶ አብራሃለይ በተባሉ የወረዳው ባለስልጣናት በተመራው ስብሰባ ላይ ወጣቶቹ ቃል የምትገቡት ሁሉ አዲስ ነገር የለውም ድርጅቱ ይሁን መንግስት ገና ህፃናት እያለን ጀምሮ ሲገባልን የነበረ የተለመደ የማታለያ ቃል ነው እየደገማችሁት ያላችሁ ሲሉ የስርአቱ ካድሬዎችን ቃል እንደተቃወሙት ለማወቅ ተችለዋል።
በወቅቱ የስርአቱ መሪዎች በሰጡት የማደናገርያ ሃሳብ። ፊት ለፊት ከተቃወሙት መካከል ወጣት በርሀ ወዲ መቃራይ በመባል የቅፅል ስም የሚታወቀውና በርከት ያሉ የአካባቢው ህብረተሰብ እንደሚገኙባቸው የገለፀው መረጃው የሸራሮ ህዝብ ጥራቱን የጠበቀ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አጥቶ በሚሰቃይበት ሰአት ለመስኖ የሚሆን ውሃ እናቀርብላችሁአለን ማለታችሁ ምን ያህል ከእውነት እንደራቃችሁ የሚያሳየን ነው ብለው መናገራቸውና ስብሰባውን ያለ ምንም ፍሬ እንደተበተነ መረጃው አክሎ አስረድተዋል።